ኢንቲርየር ዲዛይንና ብራንዲንግ

ኮካኮላ፣አዲዳስ፣ናይክ፣ማርቼዲስ፣ማክዶናልድ… እነዚህንና የመሳሰሉትን የታዋቂና ትልልቅ ድርጅቶች ስም ስንሰማ ወደ አእምሯችን የሚመጡ የድርጅቱ መገለጫ የሆኑ
የተለያዩ ምስሎች ይኖራሉ። እነዚህ ድርጅቶች አገልግሎታቸውን ያቀረቡበትና ያስተዋወቁበት መንገድ ከሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ጎላ ብለው እንዲታዩ አድርጓቸዋል። በተለያዩ ቅርንጫፍ ቦታዎች ላይ የሚኖራቸው ውስጣዊ ገፅታም ቢሆን የድርጅቱን ማንነት የሚያንፀባርቁና ለድርጅቱ ብቻ ልዩ የሆኑ ገፅታዎች ናቸው። ታድያ ብራንዲንግ ማለት ምንድን ነው? ከኢንቲርየር ዲዛይን ጋርስ ምን ያገናኘዋል?

ብራንዲንግ ማለት አንድ ድርጅት የሚያቀርባቸውን አገልግሎቶች በመለየት ድርጅቱ የሚኖረውን ማንነት ድርጅቱ በተቋቋመበት ዓላማ መሠረት መቅረፅ ማለት ነው። ይህም ድርጅቱን የሚገልፅ ስም፣ ምልክት(አርማ) ከማዘጋጀት ጀምሮ መስሪያ ቤቱ የሚኖረውን ገፅታ ዲዛይን እስከ ማድረግ ይደርሳል። አሁን አሁን እየተሻሻለ ቢመጣም በእኛ
ሀገር በስፋት ያለው ችግር የአንድ ድርጅት አርማ(logo) የተለያዩ የህትመትም ሆነ የምስል ማስታወቂያዎች ከተሠሩ በኋላ ብራንዲንጉ ያለቀ ይመስለናል። ነገር ግን ብራንዲንግ ከማስታወቅያና አርማ(logo)በዘለለ ደንበኞችላይ
የማይረሳ ስሜትን መፍጠር አለበት። ደንበኞች ወደ ድርጅታችን ሲገቡ ጀምሮ ያለውን የድርጅታችን ውስጣዊ ገፅታ ዲዛይን በጥንቃቄ በመስራት በደንበኞች ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ማጤን ያሻል።

ድርጅታችን ከተፎካካሪያቸው ለመለየት ማንነታቸውን በኢንቲርየር ዲዛይን መግለፅ ይችላሉ በዚህም ሰራተኞቻቸውን በማነቃቃትና በማሳተፍ ደንበኞቻቸውንም መያዝ ይችላሉ። አንድ ድርጅት የሚኖረውን ማንነት በውስጣዊ ገፅታው ውስጥ በምንጠቀመው ቀለም፣ የቁሳቁስ አመራረጥ እና አቀማመጥ፣ የብርሃን
አጠቃቀም ማሳየት እንችላለን። ከሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ነጥሮ ወጥቶ ለመታየትም ዲዛይኑ በጥንቃቄ መሠራት አለበት። ለምሳሌ በሀገራችን ውስጥ ብዙ የውበት መጠበቅያ ቦታዎች አሉ ነገር ግን አብዛኞቹ ተመሳሳይ የሆነ ውስጣዊ ገፅታ አላቸው። የሚጠቀሟቸው ስዕሎችና ፖስተሮች ሳይቀሩ ተመሳሳይ ናቸው።
ነገር ግን አንዳንድ የውበት መጠበቅያ ቦታዎች ለደንበኞች ምቹ አካባቢን በመፍጠር ማንነታቸውንም በዛው ያንፀባርቃሉ።

ድርጅታችን የሚኖረው ውስጣዊ ገፅታ የድርጅቱን ማንነት ከማንፀባረቁ በላይ ድርጅቱ በሚያቀርባቸው አገልግሎቶች ላይ እሴትን መጨመር ይችላል። ለምሳሌ በሀገራችን የሚገኙ የተለያዩ ሬስቶራንቶችን በምናባችሁ አስቧቸው አብዛኞቹ እምብዛም የማይለያይ የምግብ ዝርዝር ቢያቀርቡም ምግቦቹ የሚኖራቸው የዋጋ ተመን ግን በጣም
ይለያያል። ይህም የዋጋ መለያየት አገልግሎታቸውን ከሚያቀርቡበት ሁኔታ እና ስልት የመነጨ ነው። ለደንበኞቻቸው ምቾት ተጨንቀው እያንዳንዷን ውስጣዊ ገፅታ ሳቢ አድርገውና በጥንቃቄ የሚሠሩ ሬስቶራንቶች ከሌላው ቦታ የበለጠ የምግብ ዋጋ ተመን ይኖራቸዋል። ይህም በሚሠጡት አገልግሎት ላይ እሴትን በመጨመር (value add) የበለጠ ትርፋማ እንዲሆኑ ያደርጋል።

ኢንቲርየር ዲዛይን አብሮ ለመስራት የመጡ ደንበኞችን እምነት ከፍ ያደርጋል የሰራተኞችን መለዋወጥ ቁጥር ይለውጣል ከደንበኞቻቸው ጋር ያለውን ግንኙነት የድርጅቱን እሴት የሚገልፅ ይሆናል፡፡ ደንበኞች ወደ አንድ የአገልግሎት ሠጪ ተቋም ሂደው ከሚያገኙት አገልግሎት ባልተናነሰ ውስጣዊ ገፅታው ትልቅ ተፅዕኖ ያሳድርባቸዋል።
ለምሳሌ ወደ አንድ ድርጅት ደንበኞች ሲገቡ የሚኖራቸው የመጀመርያ እይታ(first impression) በጣም ተፅዕኖ ያሳድራል። የድርጅታችን ውስጣዊ ገፅታ በአግባቡ ዲዛይን ተደርጎ ሲያዩት ይዘውት የመጡትን ስራ በአግባቡ እንደምንሠራላቸው እምነት ያድርባቸዋል።

የስራ ቦታ /ቢሮ ውስጣዊ ዲዛይን

ይህን ጽሁፍ ከማንበብዎ በፊት እስኪ ስለ ስራ ቦታዎ ያስቡ። የስራ ቦታዎ ውስጣዊ ገፅታው ምን ዓይነት ስሜት ያሳድርቦታል? ዘወትር ወደ ስራ ደስ እያለዎትና ለስራ ተነሳሽ ሆነው ነው የሚሄዱት? ወይንስ ወደ ስራ መሄድዎን ሲያስቡ ማማረር ይቀናዎታል? እንግዳ ሆነውስ ወደ ሌላ ቢሮ ሲሄዱ በዚያ ቢሮ ውስጥ አይተው “ምነው ይሄ እኛ
ቢሮም በኖረ!” ያሉትና የቀኑበት ነገር አለ? በዚህ ፅሁፍ በስራ ቦታ ኢንቲርየር ዲዛይን ላይ መታሠብ ስላለባቸው ነገሮች እናያለን።

የመስርያ ቤቱ ዓላማና ግብ
እርስዎ የሚሠሩበትን ቦታ ወይንም እንግዳ ሆነው የሚሄዱበትን መስርያ ቤት ልዩ የሚያደርገው ውስጣዊ ገፅታ አለ? ስለ ድርጅቱስ በውስጣዊ ገፅታው ምን መረዳት ቻሉ? እያንዳንዱ መስርያ ቤት የተቋቋመበት የራሱ የሆኑ ዓላማና ግቦች አሉ ። እነዚህም ዓላማና ግቦች በመስርያ ቤቱ ውስጣዊ ገፅታ ላይ መንፀባረቅ አለባቸው። ይሁንና በሀገራችን ባሉ አብዛኛው መስርያ ቤቶች ይህን አናስተውልም ። በእንግዳ መቀበያ ቦታው (ሎቢው) ላይ የድርጅቱን አርማ (ሎጎ) ከማስቀመጥና በባነር የድርጅቱን ዓላማ አሳትሞ በበሩ አካባቢ ከመለጠፍ የዘለለ በውስጣዊ ገፅታው ላይ ሲንፀባረቅ አይታይም። በምንመርጠው የስራ ቦታ አቀማመጥ(space arrangment) ፣ በምንጠቀመው ቀለም፣ በምንመርጠው የግንባታ ቁሳቁስ፣ በቢሮ እቃዎች አቀማመጥና አመራረጥ ወዘተ የመስርያ ቤቱን ባህልና ማንነት ማሳየትና ልዩ የሆነ የማይረሳ ስሜት መፍጠር እንችላለን።

የሠራተኞች ብዛትና የሥራ መዋቅር
በአንድ መስርያ ቤት ውስጥ የተለያዩ የሙያ ዘርፎች እንደመኖራቸው ሊሟሉ የሚገባቸው አገልግሎቶችም እንዲሁ ይለያያሉ። ስለዚህም እያንዳንዱ የስራ ዘርፍ ምን ምን ነገሮች ያስፈልጉታል፣ የስራው ሁኔታስ እንደምን ያለ ነው የሚሉትን ነገሮች በማጥናት ወደ ዲዛይን መቀየር ያስፈልጋል።

የሠራተኞች የጋራ አገልግሎቶች
እነዚህ ቦታዎች ሠራተኞች ከስራ ሰዓት ውጪ እርስ በእርስ የሚገናኙባቸውና የሚቀራረቡባቸው እንዲሁም ስለተለያዩ
ነገሮች የሚወያዩባቸው እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ቦታዎች ናቸው።

  • የመመገብያ ስፍራዎች ፡ መስርያ ቤቶች እንዳላቸው የሠራተኛ ብዛትና የቦታ ስፋት የተለያዩ ዓይነት የመመገብያ
    ስፍራዎች ሊኖራቸው ይገባል። የዕለት ከዕለት ስራቸውን ከሚያከናውኑበት ቦታ የተለየና የመነቃቃት ስሜትን
    የሚፈጥርላቸው ቦታ ማዘጋጀት ይገባል።
  • የመፀዳጃ ቤቶች፤ በከተማችን ውስጥ ከግል ድርጅቶች ጀምሮ እስከ ትልልቅ የመንግስት መስርያ ቤቶች
    ለመጸዳጃ ቤቶች በቂ የሆነ አትኩሮት አይሰጥም። ይህም በመስርያ ቤቱ ውስጥ ያሉትን ሠራተኞችን ምቾት
    ይነሳል፣ እንግዶችንም ያጉላላል::
  • የልብስ መቀየርያና መታጠብያ ቦታዎች፡ ሠራተኞቻቸው የተለያዩ የደንብ ልብስ እንዲያደርጉ የሚፈልጉ መስርያ
    ቤቶች ለሠራተኞቻቸው በአግባቡ የተዘጋጁ የወንድና ሴቶች መቀየርያና መታጠብያ ቦታዎችን ማዘጋጀት
    አለባቸው።

ወጥነት ያለው ዲዛይን
የብዙ ድርጅቶች የፊት ለፊትና የጀርባ ገፅታ በሚያስተዛዝብ ሁኔታ እጅግ ይለያያል። “ውስጡን ለቄስ” እንዲሉ ከፊት ለፊት ያለው ቦታ ብቻ በአግባቡ ተሠርቶ የተቀረውን ከጀርባ ያለ ቦታ(ቢሮ) የመተው ባህል ይስተዋላል። በኃላፊዎችና በበታች ሠራተኞች ቢሮዎች ላይ ያለውም የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት ሠራተኞች በነፃነት ወደ አለቆቻቸው ቢሮ እንዲሄዱ አይጋብዙም። ስለዚህም ከፅዳት ሠራተኛ ጀምሮ እስከ ዋና ኃላፊ ፣ ከበር ጀምሮ እስከ ጀርባ ወጥ የሆነ ዲዛይን መስራት ይገባል። እንዲህ ምቹና ሳቢ ለስራም አመቺ የሆነ ቦታ ስንፈጥር ሠራተኞቹ ደስ ብሏቸው እንዲሰሩ ማድረግ እንችላለን።

የአካል ጉዳት ያለባቸውን ሠራተኞች/ ደንበኞች ያማከለ ዲዛይን
ከተማችን የአካል ጉዳት ላለባቸው ሠዎች እጅግ ፈታኝ የሆነች ከተማ ናት። በህንፃዎቻችንም ውስጥ ያሉት መወጣጫዎችና ሊፍቶችም ቢሆኑ ህጉ ስለሚል ብቻ ለሟሟያ የሚሠሩ እንጂ የአካል ጉዳተኞችን ምቾት ይጠብቃሉ ተብሎ ታስቦባቸው የሚሠሩ አይደሉም። በመስሪያ ቤት ውስጥም የአካል ጉዳት ላለባቸው ሠራተኞችም ሆነ እንግዶች
አመቺ የሆኑ መወጣጫዎች፣ ሰፋ ያሉ ኮሪደሮች(በስታንዳርድ የተሠሩ) ፣ አመቺ የሆኑ የመፀዳጃ ቤቶች ወዘተ· መታሠብ አለባቸው።

ለኢንቲርየር ዲዛይን የሚያስፈልግ በጀት
አብዛኛውን ግዜ ሠዎች ኢንቲርየር ዲዛይንን እንደ ቅንጦትና ከሌሎች ዕቅዶች በተረፈ ጊዜና በጀት የሚሠራ ነገር አድርገው ሲወስዱት ይስተዋላል። ነገር ግን ኢንቲርየር ዲዛይን የመስሪያ ቤቱን ማንነት የምናንፀባርቅበት ትልቅ መሳርያ እንደመሆኑ ዛሬ በባለሙያ ያሠራነው ዲዛይን ለነገ ትርፋማነታችን ትልቅ ሚናን መጫወቱ አይቀሬ ነው። ይህም የግድ ትልቅ በጀት ማዘጋጀት አለብን ማለት ሳይሆን ወደ ባለሙያ በምንሄድበት ጊዜ ከመጀመሪያው ስለ በጀታችንና ስላለን ጊዜ እውነታውን አገናዝበን እንደ አቅማችን ዲዛይን ማስደረግ ይገባል።
ቢሮና የቢሮ እቃዎች አቀማመጥ
የተለመዱት የኛ ሃገር የቢሮ ኣቀማመጦች ሰራተኞች ኣንድ ወንበርና ጠረጴዛ ተመድቦላቸው ቀኑን ሙሉ ኣንድ ቦታ ላይ ተቀምጠው እንዲውሉና እጅግ የተገታ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው የሚያስገድድ ነው:: ይህ ካካላዊና ከመንፈስ/ኣእምሮ ጤንነት ኣንፃር ኣንድምታው ብዙ ነው::
በዲዛይን ቋንቋ ሆት ዴስክ (Hot Desk) እና ዴዲኬትድ ዴስክ (Dedicated Desk )የሚባሉ የቢሮ አቀማመጦች አሉ::
ሁለቱም አይነቶች የየራሳቸው ጥሩ እና መጥፎ ጎን አላቸው ::

  • ሆት ዴስክ( Hot Desk) ማለት ሰራተኞች በግሩፕ የሚሰሩበት ቢሮ ውስጥ የፈለጉትን መቀመጫን መርጠው
    በሰዓትም ሆነ በቀን የሚሰሩበት ቦታ ነው ፡፡ ትንሽ የሰራተኛ ቅጥር ላላቸው ቦሮዎች የተመቸ ነው፡፡በተለይ
    አማካሪዎች ፣ ዲዛይነሮች ፣ ጋዜጠኞች ወዘተ እንዲህ ያለውን ዘይቤ ቢጠቀሙ ይመከራል።
  • ዴዲኬትድ ዴስክ ( Dedicated Desk ) ደግሞ የተለመደውን አይነት እያንዳንዱ ሰራተኛ የተመደበለት
    ወንበርና ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ የሚሰራበት አይነት ነው ፡፡ ይህ አይነቱ የቢሮ አቀማመጥ የማህበራዊ ግንኙነትን
    ይቀንሳል።

እነዚህ ሁለት የተለያዩ አይነት የቢሮ አቀማመጦች እንደየ ሥራው ፀባይና እንደ ድርጅቱ የስራ ባህል ዓይነት ሊተገበር
ይችላል፡፡
ስለ ስራ ቦታዎ ውስጣዊ ገፅታ ያሎትን ሀሳብ በ salome@baroqueinethiopia.com ያጋሩን።

የግድግዳ ጌጣጌጦች(ስዕሎች)

በምናባችሁ በአግባቡ ዲዛይን ተደርጎ የተሠራ ክፍል በጥራት በተሠሩ የቤት ዕቃዎች ተሞልቶ ለመሳል ሞክሩ። በጣም የሚያምር የእንጨት ወለል ላይ ውብ ቀለም ያለው ምንጣፍ፣ ምቹ የሆኑ መቀመጫዎች ፣ ልዩ ልዩ ቀለማት ያላቸው አበባዎች በጠረጴዛ ላይ ተቀምጠው አስቡ። ምንም እንኳን ክፍሉ ባማሩ ቁሳቁሶች ቢሞላም በግድግዳው ላይ ምንም ነገር ከሌለ ክፍሉ እርቃኑን የሆነና ያልተሟላ ይመስላል። “ የግድግዳ ላይ ጌጦች በተለይ ስዕል ልክ በአንድ አረፍተ ነገር ውስጥ ያለ ትክክለኛ የስርዓተ ነጥብ አጠቃቀም የፅሁፉን ሙሉ ስሜት እንደሚገልፅ ስዕልም ለአንድ ክፍል ልዩ ስሜትን ማላበስ ይችላል“። በአግባቡና በጥንቃቄ የተመረጡ ስዕሎች ለአንድ ክፍል ውበት ከማላበሳቸውም በላይ የባለቤቱን ማንነት ያንፀባርቃሉ። ቤታችሁን ወይም የስራ ቦታችሁን በስዕል የማስዋብ ሃሳብ ካላችሁ የሚከተሉትን ነጥቦች እንድታስተውሉ እመክራለሁ።

የምትገዙትን የስዕል ስራ ትርጉም ተረዱ

ሰዓሊዎች(አርቲስቶች) በስዕላቸው የተለያዩ መልዕክቶችን ያስተላልፋሉ። ነገር ግን በመጀመርያ ዕይታ ብቻ ሊያስተላልፉ የፈለጉትን መልዕክት ለመረዳት ሊያዳግተን ይችላል። ስለዚህም ሰዓሊውን (አርቲስቱን) ስለምንገዛው ስዕል ትርጉም መረዳት ተገቢ ነው።

በምርጫችሁተማመኑ

“ውበት እንደ ተመልካቹ ነው” ይባልም የለ! እናንተ ስታዩት ያማራችሁ የተረዳችሁት የጥበብ ስራ ለሌላ ሰው ትርጉም አልባና ብዙም ስሜት የማይገዛ ሊሆን ይችላል። ስታዩት ቀልባችሁ ያረፈበት ስዕል ብዙ ግዜ ትክክለኛ ምርጫ ነው። ስለዚህም ማንነታችሁን ሊገልፅ የሚችል ስዕል ከመምረጥ ወደኋላ አትበሉ።

ከስዕል ውጪ ሌሎች ጌጣጌጦችን መጠቀም እንደምትችሉአትዘንጉ

ብዙ ሰዎች ስዕልን የቅንጦትና እጅግ ውድ ነገር አድርገው ስለሚያስቡት በቤታቸው ለመስቀል አይደፍሩም። ነገር ግን በግድግዳችን ላይ የምንሰቅላቸው ስዕሎች ብቻ ሳይሆኑ ፎቶግራፎች፤ ልዩ ልዩ ቅርፃ ቅርፃችና የእጅ ስራዎች ሊሆኑ ይችላሉ። አደራደራቸውንና ለክፉሉ የሚሰጡትን ስሜት በማስተዋል ቀልብ ሳቢ የሆነ ዲዛይን መፍጠር ይቻላል።

ስዕሉንየምታስቀምጡበትንቦታአዘጋጁ

አንድን ስዕል ወደ ቤታችሁ ይዛችሁ ከመምጣታችሁ በፊት ስዕሉ የሚቀመጥበትን ቦታ ወስኑ። ስዕልን በአብዛኛው እንደ የክፍሉ አትኩሮት ቦታ (focal point) ስለምንጠቀመው በአካባቢው ያሉትን የዕቃዎች አቀማመጥ ማስተካከል አትርሱ። በተጨማሪም ለስዕሉ ተስማሚና ቀልብን ሊስብ የሚችል የብርሃን አጠቃቀም ምረጡ።

የተለያዩ አማራጮችን ተመልከቱ

የምትመርጡት ስዕል የግድ ከክፍሉ ጋር መመሳሰል የለበትም። ስዕሎች እጅግ በተለያዩ ቅርፆችና ዲዛይኖች ስለሚሠራ የተለያዩ አማራጮችን ማየት ይመከራል። ለምሳሌ በጣም ዘመናዊ የሆነ ክፍል በባህላዊ ስዕሎች ማስጌጥ ይቻላል። እንደዚሁም ደግሞ ባህላዊ የሆነ ክፍል በዘመናዊ ስዕሎች ማስጌጥ ይቻላል፡ ሁለቱንም በማደባለቅ ደግሞ የተሻለ ውበትን ማግኘት እንችላለን።

የወለል ሽፋን አመራረጥ በቤት ውስጥ ዲዛይን የቤት

የቤት ውስጥ ዲዛይን ከሚያካትታቸው ነገሮች ውስጥ በጥቂቱ የቀለም ምርጫ ፣ የብርሃን (መብራት ) አጠቃቀም፣ የቤት ውስጥ መገልገያና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች አመራረጥና አጠቃቀም ፣ የወለልና የጣርያ ሽፋን አመራረጥ ይገኙበታል ። የወለል ሽፋን ማለት የአንድ ህንፃ መሠረታዊ መዋቅር (structure) ከተጨረሰ በኋላ ወለሉ ለአጠቃቀም ምቹ እንዲሆን በወለሉ ላይ የሚነጠፍ ማንኛውም አይነት ቁሳቁስ ነው። ለተሠራው ዲዛይን አግባብ የሆነና ለአጠቃቀምም ምቹ የሆነ የወለል ሽፋን ለመምረጥ ያስችለን ዘንድ እነዚህን ነጥቦች ማገናዘብ አስፈላጊ ነው።

ህንፃው ወይም ቤቱ ከተሠራበት የዲዛይን ሃሳብ ጋር የተመረጠው የወለል ሽፋን አግባብነት
የተመረጠው ዕቃ ጥንካሬ
የወለል ሽፋኑን የምንጠቀምበት የክፍል ወይም የአገልግሎት አይነት ( ለሳሎን፣ለመኝታ ቤት፣ ለመታጠብያ ቤት፣ ለመሰብሰብያ አዳራሽ፣ ለህክምና ቦታ …… )
የተመረጠው የወለል ሽፋን በአካባቢው ካለው የአየር ንብረት ጋር የሚስማማ መሆኑ

የቤት ውስጥ ዲዛይነር/ኢንተርየር ዲዛይነር ማለት ምን ማለት ነው?

የቤት ውስጥ ዲዛይነሮች የፈጠራ ባለሙያ፤ምስል ፈጣሪዋች እና የስነ ጥበብ ባለሙያዋች ናቸው፡፡ የቤት ውስጥ ዲዛይን ስንል ደግሞ የመኖሪያና የንግድ/የስራ ቦታ ብለን በሁለት ግሩፕ ልንከፍላቸው እንችላለን። በተጨማሪምየቤት ውስጥ ዲዛይነሮች ስነ ምግባር ያላቸው፤ የተቀናጁ እና ክህሎት ያላቸው የስራ ሰዎች ናቸው፡፡ ከስነ-ውበት እይታ ጋር ዕውቀቶችን በማዋሀድ ከደንበኞች እና ከሌሎች የዲዛይን ባለሙዎች ጋር በመሆን ምቹ፤ ተግባራዊ፤ ሳቢ፤ እና ለክፍተቶች መፍትሔ በመፍጥርና በመጠቀም የሰዎችን ፍላጎት የሚያማልሉ የዲዛይን አማራጮችን ያዘጋጃሉ፡፡

በሌሎች ስራዎች እንደሚታየው ጠንካራ ስራ ከታከለበት የቤት ውስጥ ዲዛይን ስራ ውጤታማ እና አስደሳች ይሆናል፡፡ በቤት ውስጥ ዲዛይን ስራ ለመላቅ የቴክኒክ እውቀት፤ ከተለመደእይታ ወጣ ያለ አዲስ ሀሳብ ማፍለቅ እና ትጋትን ይጠይቃል፡፡

የተዋጣለት ዲዛይነር ለመሆን የስኬት ቁልፎች

እንደ ማንኛውም ስነ ጥበብ ባለሙያ የቤት ውስጥ ዲዛይነሮች ከገንዘብገቢ የበለጠ ደንበኞቻችውን በማርካት ይደስታሉ፡፡ስለዚህም ስነ-ጥበባዊ እና የፕሮጀክት ቴክኒክ መስፈርቶችን፤ ከሰዎች ጋር መግባባትን እና የስራ አመራር ዘዴዎችን ሊረዱ ይገባል፡፡

ስነ-ጥበባዊ እና የቴክኒክ መስፈርቶች

የቤት ውስጥ ዲዛይነሮች ክፍተቶችን እንዴት በእቅድ ውስጥ ማስገባት እንዳለባቸው እና ለደንበኞች ጥሩ ሆኖ እንዲቀርብላቸው እቅዱን በምስል ማቅረብ ማወቅ አለባቸው፡፡ ከምስል በተጨማሪም ሀሳባቸውን በደንብ የመግለፅ ችሎታ ይጠበቅባቸዋል። እንደዚሁም ለዲዛይን የተመረጡት ክፍሎች ላይ የዲዛይን ስራዎችን ለማከናወን የሚጠቀሙባቸውን ቁሳቁሶች እና ምርቶች ማወቅ፣ ለውስጣዊ ዲዛይን ሰራ ኮንትራቶችን፣ ለግዢ የሚያስፈልጉ ፓኬጆችንእና የግንባታ ሰነዶችን እና ዝርዝሮችን ማዘጋጀትየሚጠበቅባቸው ሲሆን በተጨማሪም ገፅታ፤ ቀለም፤ መብራት/ብርሃን እና ሌሎች ተጓዳኝ ጉዳዮች ተቀናጅተው እና ህብር ፈጥረው ክፍሉን እንዴት እንደሚያስውቡት ሊያውቁት ይገባል፡፡ እንደዚሁምየጤና እና የምቾት ጉዳዮችን፤ የህንፃ ኮዶችን፣ መዋቀራዊ መስፈርቶች እና በርካታ የቴክኒክ ጉዳዬችን ሊረዱ የገባል፡፡

ከሰዎች ጋራ የመግባባት ክህሎት

የቤት ውስጥ ዲዛይነሮች ከበርካታ አይነት ሰዎች ጋር መስተጋብር በመፍጠር ሂደት እና በውይይቱ ሂደት ላይ ምቹ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በግልፅ እና በውጤታማነት እንዲሁም በጥንቃቄ በማዳመጥ ከሰዎች ጋር ሊግባቡ ይገባል፡፡ ምክንያቱም በአብዛኛው ጊዜ ከአርክቴቶች፤ ተቋራጮች እና ሌሎች የአገልገሎት አቅራቢዎች ጋራ ሊሰሩ ስለሚያስፈለግ የቤት ውስጥ ዲዛይነሮች የቡድን መሪዎች እና መልካም የቡድን አጋሮች ሊሆኑ ይገባል፡፡ ችግሮችን ለመፍታት በሚፍለግበት ግዜም ለመደራደር እና ለመታረቅ ፈቃደኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

የስራ አመራር ዘዴዎች

የቤት ውስጥ ዲዛይነሮች በተከታታይ ከአንድ ፕሮጀክት በላይ በአንድ ግዜ በአስቸካይ የጊዜ ቀጠሮዎች ስለሚሰሩ የጊዜ እና የፕሮጀክት ስራ አመራር ክህሎት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የቤት ውስጥ ዲዛይነሮች የስራ እቅድ ሊረዱ እና ሀሳቦቻቸውን ለደንበኞች የመሸጥ፤ መረጃ ሰጪ እና አሳማኝ ፕሮፖዛሎችን የመስራት እና ስራዎችን የማቅረብ እና መልካም የደንበኛ መስተጋብሮችን የመፍጠር መረዳቱ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

በስሎሜ ከባሮክ ኢንተርየርስ እና ኢቬንትስ