ኢንቲርየር ዲዛይንና ብራንዲንግ

ኮካኮላ፣አዲዳስ፣ናይክ፣ማርቼዲስ፣ማክዶናልድ… እነዚህንና የመሳሰሉትን የታዋቂና ትልልቅ ድርጅቶች ስም ስንሰማ ወደ አእምሯችን የሚመጡ የድርጅቱ መገለጫ የሆኑ
የተለያዩ ምስሎች ይኖራሉ። እነዚህ ድርጅቶች አገልግሎታቸውን ያቀረቡበትና ያስተዋወቁበት መንገድ ከሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ጎላ ብለው እንዲታዩ አድርጓቸዋል። በተለያዩ ቅርንጫፍ ቦታዎች ላይ የሚኖራቸው ውስጣዊ ገፅታም ቢሆን የድርጅቱን ማንነት የሚያንፀባርቁና ለድርጅቱ ብቻ ልዩ የሆኑ ገፅታዎች ናቸው። ታድያ ብራንዲንግ ማለት ምንድን ነው? ከኢንቲርየር ዲዛይን ጋርስ ምን ያገናኘዋል?

ብራንዲንግ ማለት አንድ ድርጅት የሚያቀርባቸውን አገልግሎቶች በመለየት ድርጅቱ የሚኖረውን ማንነት ድርጅቱ በተቋቋመበት ዓላማ መሠረት መቅረፅ ማለት ነው። ይህም ድርጅቱን የሚገልፅ ስም፣ ምልክት(አርማ) ከማዘጋጀት ጀምሮ መስሪያ ቤቱ የሚኖረውን ገፅታ ዲዛይን እስከ ማድረግ ይደርሳል። አሁን አሁን እየተሻሻለ ቢመጣም በእኛ
ሀገር በስፋት ያለው ችግር የአንድ ድርጅት አርማ(logo) የተለያዩ የህትመትም ሆነ የምስል ማስታወቂያዎች ከተሠሩ በኋላ ብራንዲንጉ ያለቀ ይመስለናል። ነገር ግን ብራንዲንግ ከማስታወቅያና አርማ(logo)በዘለለ ደንበኞችላይ
የማይረሳ ስሜትን መፍጠር አለበት። ደንበኞች ወደ ድርጅታችን ሲገቡ ጀምሮ ያለውን የድርጅታችን ውስጣዊ ገፅታ ዲዛይን በጥንቃቄ በመስራት በደንበኞች ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ማጤን ያሻል።

ድርጅታችን ከተፎካካሪያቸው ለመለየት ማንነታቸውን በኢንቲርየር ዲዛይን መግለፅ ይችላሉ በዚህም ሰራተኞቻቸውን በማነቃቃትና በማሳተፍ ደንበኞቻቸውንም መያዝ ይችላሉ። አንድ ድርጅት የሚኖረውን ማንነት በውስጣዊ ገፅታው ውስጥ በምንጠቀመው ቀለም፣ የቁሳቁስ አመራረጥ እና አቀማመጥ፣ የብርሃን
አጠቃቀም ማሳየት እንችላለን። ከሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ነጥሮ ወጥቶ ለመታየትም ዲዛይኑ በጥንቃቄ መሠራት አለበት። ለምሳሌ በሀገራችን ውስጥ ብዙ የውበት መጠበቅያ ቦታዎች አሉ ነገር ግን አብዛኞቹ ተመሳሳይ የሆነ ውስጣዊ ገፅታ አላቸው። የሚጠቀሟቸው ስዕሎችና ፖስተሮች ሳይቀሩ ተመሳሳይ ናቸው።
ነገር ግን አንዳንድ የውበት መጠበቅያ ቦታዎች ለደንበኞች ምቹ አካባቢን በመፍጠር ማንነታቸውንም በዛው ያንፀባርቃሉ።

ድርጅታችን የሚኖረው ውስጣዊ ገፅታ የድርጅቱን ማንነት ከማንፀባረቁ በላይ ድርጅቱ በሚያቀርባቸው አገልግሎቶች ላይ እሴትን መጨመር ይችላል። ለምሳሌ በሀገራችን የሚገኙ የተለያዩ ሬስቶራንቶችን በምናባችሁ አስቧቸው አብዛኞቹ እምብዛም የማይለያይ የምግብ ዝርዝር ቢያቀርቡም ምግቦቹ የሚኖራቸው የዋጋ ተመን ግን በጣም
ይለያያል። ይህም የዋጋ መለያየት አገልግሎታቸውን ከሚያቀርቡበት ሁኔታ እና ስልት የመነጨ ነው። ለደንበኞቻቸው ምቾት ተጨንቀው እያንዳንዷን ውስጣዊ ገፅታ ሳቢ አድርገውና በጥንቃቄ የሚሠሩ ሬስቶራንቶች ከሌላው ቦታ የበለጠ የምግብ ዋጋ ተመን ይኖራቸዋል። ይህም በሚሠጡት አገልግሎት ላይ እሴትን በመጨመር (value add) የበለጠ ትርፋማ እንዲሆኑ ያደርጋል።

ኢንቲርየር ዲዛይን አብሮ ለመስራት የመጡ ደንበኞችን እምነት ከፍ ያደርጋል የሰራተኞችን መለዋወጥ ቁጥር ይለውጣል ከደንበኞቻቸው ጋር ያለውን ግንኙነት የድርጅቱን እሴት የሚገልፅ ይሆናል፡፡ ደንበኞች ወደ አንድ የአገልግሎት ሠጪ ተቋም ሂደው ከሚያገኙት አገልግሎት ባልተናነሰ ውስጣዊ ገፅታው ትልቅ ተፅዕኖ ያሳድርባቸዋል።
ለምሳሌ ወደ አንድ ድርጅት ደንበኞች ሲገቡ የሚኖራቸው የመጀመርያ እይታ(first impression) በጣም ተፅዕኖ ያሳድራል። የድርጅታችን ውስጣዊ ገፅታ በአግባቡ ዲዛይን ተደርጎ ሲያዩት ይዘውት የመጡትን ስራ በአግባቡ እንደምንሠራላቸው እምነት ያድርባቸዋል።