የግድግዳ ጌጣጌጦች(ስዕሎች)

በምናባችሁ በአግባቡ ዲዛይን ተደርጎ የተሠራ ክፍል በጥራት በተሠሩ የቤት ዕቃዎች ተሞልቶ ለመሳል ሞክሩ። በጣም የሚያምር የእንጨት ወለል ላይ ውብ ቀለም ያለው ምንጣፍ፣ ምቹ የሆኑ መቀመጫዎች ፣ ልዩ ልዩ ቀለማት ያላቸው አበባዎች በጠረጴዛ ላይ ተቀምጠው አስቡ። ምንም እንኳን ክፍሉ ባማሩ ቁሳቁሶች ቢሞላም በግድግዳው ላይ ምንም ነገር ከሌለ ክፍሉ እርቃኑን የሆነና ያልተሟላ ይመስላል። “ የግድግዳ ላይ ጌጦች በተለይ ስዕል ልክ በአንድ አረፍተ ነገር ውስጥ ያለ ትክክለኛ የስርዓተ ነጥብ አጠቃቀም የፅሁፉን ሙሉ ስሜት እንደሚገልፅ ስዕልም ለአንድ ክፍል ልዩ ስሜትን ማላበስ ይችላል“። በአግባቡና በጥንቃቄ የተመረጡ ስዕሎች ለአንድ ክፍል ውበት ከማላበሳቸውም በላይ የባለቤቱን ማንነት ያንፀባርቃሉ። ቤታችሁን ወይም የስራ ቦታችሁን በስዕል የማስዋብ ሃሳብ ካላችሁ የሚከተሉትን ነጥቦች እንድታስተውሉ እመክራለሁ።

የምትገዙትን የስዕል ስራ ትርጉም ተረዱ

ሰዓሊዎች(አርቲስቶች) በስዕላቸው የተለያዩ መልዕክቶችን ያስተላልፋሉ። ነገር ግን በመጀመርያ ዕይታ ብቻ ሊያስተላልፉ የፈለጉትን መልዕክት ለመረዳት ሊያዳግተን ይችላል። ስለዚህም ሰዓሊውን (አርቲስቱን) ስለምንገዛው ስዕል ትርጉም መረዳት ተገቢ ነው።

በምርጫችሁተማመኑ

“ውበት እንደ ተመልካቹ ነው” ይባልም የለ! እናንተ ስታዩት ያማራችሁ የተረዳችሁት የጥበብ ስራ ለሌላ ሰው ትርጉም አልባና ብዙም ስሜት የማይገዛ ሊሆን ይችላል። ስታዩት ቀልባችሁ ያረፈበት ስዕል ብዙ ግዜ ትክክለኛ ምርጫ ነው። ስለዚህም ማንነታችሁን ሊገልፅ የሚችል ስዕል ከመምረጥ ወደኋላ አትበሉ።

ከስዕል ውጪ ሌሎች ጌጣጌጦችን መጠቀም እንደምትችሉአትዘንጉ

ብዙ ሰዎች ስዕልን የቅንጦትና እጅግ ውድ ነገር አድርገው ስለሚያስቡት በቤታቸው ለመስቀል አይደፍሩም። ነገር ግን በግድግዳችን ላይ የምንሰቅላቸው ስዕሎች ብቻ ሳይሆኑ ፎቶግራፎች፤ ልዩ ልዩ ቅርፃ ቅርፃችና የእጅ ስራዎች ሊሆኑ ይችላሉ። አደራደራቸውንና ለክፉሉ የሚሰጡትን ስሜት በማስተዋል ቀልብ ሳቢ የሆነ ዲዛይን መፍጠር ይቻላል።

ስዕሉንየምታስቀምጡበትንቦታአዘጋጁ

አንድን ስዕል ወደ ቤታችሁ ይዛችሁ ከመምጣታችሁ በፊት ስዕሉ የሚቀመጥበትን ቦታ ወስኑ። ስዕልን በአብዛኛው እንደ የክፍሉ አትኩሮት ቦታ (focal point) ስለምንጠቀመው በአካባቢው ያሉትን የዕቃዎች አቀማመጥ ማስተካከል አትርሱ። በተጨማሪም ለስዕሉ ተስማሚና ቀልብን ሊስብ የሚችል የብርሃን አጠቃቀም ምረጡ።

የተለያዩ አማራጮችን ተመልከቱ

የምትመርጡት ስዕል የግድ ከክፍሉ ጋር መመሳሰል የለበትም። ስዕሎች እጅግ በተለያዩ ቅርፆችና ዲዛይኖች ስለሚሠራ የተለያዩ አማራጮችን ማየት ይመከራል። ለምሳሌ በጣም ዘመናዊ የሆነ ክፍል በባህላዊ ስዕሎች ማስጌጥ ይቻላል። እንደዚሁም ደግሞ ባህላዊ የሆነ ክፍል በዘመናዊ ስዕሎች ማስጌጥ ይቻላል፡ ሁለቱንም በማደባለቅ ደግሞ የተሻለ ውበትን ማግኘት እንችላለን።