የስራ ቦታ /ቢሮ ውስጣዊ ዲዛይን

ይህን ጽሁፍ ከማንበብዎ በፊት እስኪ ስለ ስራ ቦታዎ ያስቡ። የስራ ቦታዎ ውስጣዊ ገፅታው ምን ዓይነት ስሜት ያሳድርቦታል? ዘወትር ወደ ስራ ደስ እያለዎትና ለስራ ተነሳሽ ሆነው ነው የሚሄዱት? ወይንስ ወደ ስራ መሄድዎን ሲያስቡ ማማረር ይቀናዎታል? እንግዳ ሆነውስ ወደ ሌላ ቢሮ ሲሄዱ በዚያ ቢሮ ውስጥ አይተው “ምነው ይሄ እኛ
ቢሮም በኖረ!” ያሉትና የቀኑበት ነገር አለ? በዚህ ፅሁፍ በስራ ቦታ ኢንቲርየር ዲዛይን ላይ መታሠብ ስላለባቸው ነገሮች እናያለን።

የመስርያ ቤቱ ዓላማና ግብ
እርስዎ የሚሠሩበትን ቦታ ወይንም እንግዳ ሆነው የሚሄዱበትን መስርያ ቤት ልዩ የሚያደርገው ውስጣዊ ገፅታ አለ? ስለ ድርጅቱስ በውስጣዊ ገፅታው ምን መረዳት ቻሉ? እያንዳንዱ መስርያ ቤት የተቋቋመበት የራሱ የሆኑ ዓላማና ግቦች አሉ ። እነዚህም ዓላማና ግቦች በመስርያ ቤቱ ውስጣዊ ገፅታ ላይ መንፀባረቅ አለባቸው። ይሁንና በሀገራችን ባሉ አብዛኛው መስርያ ቤቶች ይህን አናስተውልም ። በእንግዳ መቀበያ ቦታው (ሎቢው) ላይ የድርጅቱን አርማ (ሎጎ) ከማስቀመጥና በባነር የድርጅቱን ዓላማ አሳትሞ በበሩ አካባቢ ከመለጠፍ የዘለለ በውስጣዊ ገፅታው ላይ ሲንፀባረቅ አይታይም። በምንመርጠው የስራ ቦታ አቀማመጥ(space arrangment) ፣ በምንጠቀመው ቀለም፣ በምንመርጠው የግንባታ ቁሳቁስ፣ በቢሮ እቃዎች አቀማመጥና አመራረጥ ወዘተ የመስርያ ቤቱን ባህልና ማንነት ማሳየትና ልዩ የሆነ የማይረሳ ስሜት መፍጠር እንችላለን።

የሠራተኞች ብዛትና የሥራ መዋቅር
በአንድ መስርያ ቤት ውስጥ የተለያዩ የሙያ ዘርፎች እንደመኖራቸው ሊሟሉ የሚገባቸው አገልግሎቶችም እንዲሁ ይለያያሉ። ስለዚህም እያንዳንዱ የስራ ዘርፍ ምን ምን ነገሮች ያስፈልጉታል፣ የስራው ሁኔታስ እንደምን ያለ ነው የሚሉትን ነገሮች በማጥናት ወደ ዲዛይን መቀየር ያስፈልጋል።

የሠራተኞች የጋራ አገልግሎቶች
እነዚህ ቦታዎች ሠራተኞች ከስራ ሰዓት ውጪ እርስ በእርስ የሚገናኙባቸውና የሚቀራረቡባቸው እንዲሁም ስለተለያዩ
ነገሮች የሚወያዩባቸው እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ቦታዎች ናቸው።

  • የመመገብያ ስፍራዎች ፡ መስርያ ቤቶች እንዳላቸው የሠራተኛ ብዛትና የቦታ ስፋት የተለያዩ ዓይነት የመመገብያ
    ስፍራዎች ሊኖራቸው ይገባል። የዕለት ከዕለት ስራቸውን ከሚያከናውኑበት ቦታ የተለየና የመነቃቃት ስሜትን
    የሚፈጥርላቸው ቦታ ማዘጋጀት ይገባል።
  • የመፀዳጃ ቤቶች፤ በከተማችን ውስጥ ከግል ድርጅቶች ጀምሮ እስከ ትልልቅ የመንግስት መስርያ ቤቶች
    ለመጸዳጃ ቤቶች በቂ የሆነ አትኩሮት አይሰጥም። ይህም በመስርያ ቤቱ ውስጥ ያሉትን ሠራተኞችን ምቾት
    ይነሳል፣ እንግዶችንም ያጉላላል::
  • የልብስ መቀየርያና መታጠብያ ቦታዎች፡ ሠራተኞቻቸው የተለያዩ የደንብ ልብስ እንዲያደርጉ የሚፈልጉ መስርያ
    ቤቶች ለሠራተኞቻቸው በአግባቡ የተዘጋጁ የወንድና ሴቶች መቀየርያና መታጠብያ ቦታዎችን ማዘጋጀት
    አለባቸው።

ወጥነት ያለው ዲዛይን
የብዙ ድርጅቶች የፊት ለፊትና የጀርባ ገፅታ በሚያስተዛዝብ ሁኔታ እጅግ ይለያያል። “ውስጡን ለቄስ” እንዲሉ ከፊት ለፊት ያለው ቦታ ብቻ በአግባቡ ተሠርቶ የተቀረውን ከጀርባ ያለ ቦታ(ቢሮ) የመተው ባህል ይስተዋላል። በኃላፊዎችና በበታች ሠራተኞች ቢሮዎች ላይ ያለውም የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት ሠራተኞች በነፃነት ወደ አለቆቻቸው ቢሮ እንዲሄዱ አይጋብዙም። ስለዚህም ከፅዳት ሠራተኛ ጀምሮ እስከ ዋና ኃላፊ ፣ ከበር ጀምሮ እስከ ጀርባ ወጥ የሆነ ዲዛይን መስራት ይገባል። እንዲህ ምቹና ሳቢ ለስራም አመቺ የሆነ ቦታ ስንፈጥር ሠራተኞቹ ደስ ብሏቸው እንዲሰሩ ማድረግ እንችላለን።

የአካል ጉዳት ያለባቸውን ሠራተኞች/ ደንበኞች ያማከለ ዲዛይን
ከተማችን የአካል ጉዳት ላለባቸው ሠዎች እጅግ ፈታኝ የሆነች ከተማ ናት። በህንፃዎቻችንም ውስጥ ያሉት መወጣጫዎችና ሊፍቶችም ቢሆኑ ህጉ ስለሚል ብቻ ለሟሟያ የሚሠሩ እንጂ የአካል ጉዳተኞችን ምቾት ይጠብቃሉ ተብሎ ታስቦባቸው የሚሠሩ አይደሉም። በመስሪያ ቤት ውስጥም የአካል ጉዳት ላለባቸው ሠራተኞችም ሆነ እንግዶች
አመቺ የሆኑ መወጣጫዎች፣ ሰፋ ያሉ ኮሪደሮች(በስታንዳርድ የተሠሩ) ፣ አመቺ የሆኑ የመፀዳጃ ቤቶች ወዘተ· መታሠብ አለባቸው።

ለኢንቲርየር ዲዛይን የሚያስፈልግ በጀት
አብዛኛውን ግዜ ሠዎች ኢንቲርየር ዲዛይንን እንደ ቅንጦትና ከሌሎች ዕቅዶች በተረፈ ጊዜና በጀት የሚሠራ ነገር አድርገው ሲወስዱት ይስተዋላል። ነገር ግን ኢንቲርየር ዲዛይን የመስሪያ ቤቱን ማንነት የምናንፀባርቅበት ትልቅ መሳርያ እንደመሆኑ ዛሬ በባለሙያ ያሠራነው ዲዛይን ለነገ ትርፋማነታችን ትልቅ ሚናን መጫወቱ አይቀሬ ነው። ይህም የግድ ትልቅ በጀት ማዘጋጀት አለብን ማለት ሳይሆን ወደ ባለሙያ በምንሄድበት ጊዜ ከመጀመሪያው ስለ በጀታችንና ስላለን ጊዜ እውነታውን አገናዝበን እንደ አቅማችን ዲዛይን ማስደረግ ይገባል።
ቢሮና የቢሮ እቃዎች አቀማመጥ
የተለመዱት የኛ ሃገር የቢሮ ኣቀማመጦች ሰራተኞች ኣንድ ወንበርና ጠረጴዛ ተመድቦላቸው ቀኑን ሙሉ ኣንድ ቦታ ላይ ተቀምጠው እንዲውሉና እጅግ የተገታ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው የሚያስገድድ ነው:: ይህ ካካላዊና ከመንፈስ/ኣእምሮ ጤንነት ኣንፃር ኣንድምታው ብዙ ነው::
በዲዛይን ቋንቋ ሆት ዴስክ (Hot Desk) እና ዴዲኬትድ ዴስክ (Dedicated Desk )የሚባሉ የቢሮ አቀማመጦች አሉ::
ሁለቱም አይነቶች የየራሳቸው ጥሩ እና መጥፎ ጎን አላቸው ::

  • ሆት ዴስክ( Hot Desk) ማለት ሰራተኞች በግሩፕ የሚሰሩበት ቢሮ ውስጥ የፈለጉትን መቀመጫን መርጠው
    በሰዓትም ሆነ በቀን የሚሰሩበት ቦታ ነው ፡፡ ትንሽ የሰራተኛ ቅጥር ላላቸው ቦሮዎች የተመቸ ነው፡፡በተለይ
    አማካሪዎች ፣ ዲዛይነሮች ፣ ጋዜጠኞች ወዘተ እንዲህ ያለውን ዘይቤ ቢጠቀሙ ይመከራል።
  • ዴዲኬትድ ዴስክ ( Dedicated Desk ) ደግሞ የተለመደውን አይነት እያንዳንዱ ሰራተኛ የተመደበለት
    ወንበርና ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ የሚሰራበት አይነት ነው ፡፡ ይህ አይነቱ የቢሮ አቀማመጥ የማህበራዊ ግንኙነትን
    ይቀንሳል።

እነዚህ ሁለት የተለያዩ አይነት የቢሮ አቀማመጦች እንደየ ሥራው ፀባይና እንደ ድርጅቱ የስራ ባህል ዓይነት ሊተገበር
ይችላል፡፡
ስለ ስራ ቦታዎ ውስጣዊ ገፅታ ያሎትን ሀሳብ በ salome@baroqueinethiopia.com ያጋሩን።